" በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈ ሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው " - ቅዱስነታቸው
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2016 ዓመተ ምሕረት የዘመን መለወጫን በማስመልከት አባታዊ ቃለ በረከት አስተላለፉ።
ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦
" ... ያለፈው ዓመት ያሳረፈብንን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በሚገባ አስተውለን፣ ዳግም ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገርብን ካላደረግን አዲሱ ዓመት ለኛ የሚሰጠን ትርጉም ምንድን ነው ?
ባለፉት ዓመታት በሃይማኖት፣ በባህል በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሕዝባችን ሥር የሰደደውን የእርስ በርስ መጠራጠር ከልብ መርምረን ወደ ድሮው እኛነታችን ካልተመለከትንስ አዲስ ዘመን እያልን ማክበራችን ምን ፋይዳ አለው ?
ይህንን ሁሉ በአዲሱ ዓመት በማጤን ያለፈውን ጎጂ ነገር በመተው፤ ጠቃሚውን ግን ይበልጥ በማጠናከር አዲሱን ዓመት መቀበል አለብን።
ከሁሉ በላይ ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመው ምንድነው ? በሚለው በምር መስራት አለብን፤ በመለያየት፣ በመፎካከር፣ በመበቃቀል፣ በመናናቅ፣ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ በመጣር፣ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ኃይልን በመጠቀም፣ የሕዝብን ጥቅም ማስከበርና የሀገርን አንድነት ማስቀጠል አይቻልም ፤ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ዕመቀ ዕመቅ እየከተቱ ያሉ እንደዚህ ያሉ አስተሳሰቦች ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ ከአሮጌው ዓመት ጋራ አብረው መወገድ አለባቸው።
በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈ ሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው፤ ችግሮችን በውይይት፣ አሊያም በሕግ እየተፈቱ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ነጻነትና አንድነት መረጋገጥ አለበት፤ ሀገርንና ሕዝብን ለዘለቄታው በአንድነት የሚያስቀጥሉ የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ፣ የተጐዳውን መደገፍ፣ ሆድ የባሰውን ማለዘብ፣ የተጠቃውን ማጽናናት ሲቻል ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት ይህንን ለማድረግ በቊርጥ ከተነሣን ሰላማችን ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሀገራችንም በበረከት ትሞላለች፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችን ሁሉ ይህንን ጥሪያችንን ተቀብላችሁ የጥፋት መሳሪያችሁንም አስቀምጣችሁ ወደ ሰላም ማእድ ቀርባችሁ በወንድማማችነት መንፈስ ችግራችሁን በክብ ጠረጴዛ በውይይት በመፍታት የሀገሪቱንና የሕዝቡን አንድነት እንድታስቀጥሉ ሁሉን በሚያይ እግዚአብሔር ስም እንማጸናችኋለን፡፡ "



