“ክትባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልገናል” ቢል ጌትስ

Comments · 829 Views

“ክትባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልገናል” ቢል ጌትስ

አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ለኮሮናቫይረስ ክትባት ሲገኝ በመላው ዓለም መከፋፈል አለበት አሉ።

የዓለም መሪዎች፣ ሀብታም ድርጅቶችና ግለሰቦች ክትባትን በተመለከተ በበይነ መረብ ውይይት ያደርጋሉ። ለክትባት ምርት የሚውል 7.4 ቢሊዮን ዶላር ያሰባስባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ቢል ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “ለክትባት የሚደረግ ድጋፍ ከመቼውም በላይ አሁን ያስፈልገናል” ብለው እያንዳንዱ እርዳታ ሕይወት እንደሚያተርፍ አስረግጠዋል።

የሚሰባሰበው ገንዘብ ውጤታማ የሆነ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለድሃ አገራት ለማከፋፈል ይውላል። እንደ ፖሊዮ፣ ታይፎይድ እና ኩፍኝ ያሉ ገዳይ በሽታዎችን ለመከላከልም ይውላል።

የወረርሽኙ ሥርጭት በመላው ዓለም ለክትባት የሚደረገውን ድጋፍ አደናቅፏል። በዚህ ምክንያት ወደ 80 ሚሊዮን ሕፃናት መደበኛ ክትባት ሳያገኙ ቀርተዋል።

ቢልየነሩ እንዳሉት፤ ስለ ክትባቲ የሚናፈሰው ሐሰተኛ ወሬ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ላይ አጥልቷል።

“ክትባቱን ስናገኝ ከ80 በመቶ በላይ ሕዝቡ እንዲወስደው በማድረግ ማኅበረሰባዊ በሽታውን የመከላከል አቅም (herd immunity) ማዳበር እንፈልጋለን” ብለዋል።

“ክትባቱ መጥፎ ነው። ከጀርባው ሴራ አለ ከተባለ ግን ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ፍቃደኛ አይሆኑም። በሽታው ሰዎችን መቅጠፉንም ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።

BBC News Amharic

Comments