በሊባኖስ ለሽያጭ ቀርባ የነበረችው ናይጄሪያዊት ወደ ሃገሯ አልመለስም አለች

Comments · 780 Views

በሊባኖስ ለሽያጭ ቀርባ የነበረችው ናይጄሪያዊት ወደ ሃገሯ አልመለስም አለች

በሊባኖስ ባለፈው ወር ለሽያጭ ቀርባ የነበረችው ናይጄሪያዊት ወደ ሃገሯ እንደማትመለስ መግለጿን የናይጄሪያ ዲያስፖራ ኮሚሽን አስታውቋል። ግለሰቧ ለሽያጭ የቀረበችው በፌስቡክ ላይ በወጣ ማስታወቂያ ነበር። ግለሰቧንም ለመግዛት የቀረበው የገንዘብ መጠን አንድ ሺ ዶላር ነበር።

ከመሸጧም በፊት የሊባኖስ ባለስልጣናት ያዳኗት ሲሆን በቤይሩት ወደሚገኘው የናይጄሪያ ኤምባሲም ወስደዋት ነበር።

በማስታወቂያው ላይም የግለሰቧ የፓስፖርት ፎቶ በግልፅ የሚታይ ሲሆን በርካታ ሰዎች መጋራታቸውን ተከትሎም፤ ቁጣና ውግዘትም አስተናግዷል።

በማስታወቂያው ተሳትፏል የተባለው ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል።

የ30 አመቷ ናይጄሪያዊት በሊባኖስ ሌላ ስራ እንዳገኘችም አስታውቃለች።

የዲያስፖራ ኮሚሽን አቢኬ ዳቢሪ ኤሬዋ እንደተናገሩት ወደ ሃገሯ እንድትመለስ ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም በእምቢተኝነቷ መፅናቷን ነው።

"የትውልድ ቦታዋ ኦዮ ግዛት ባለስልጣን በስልክ እንድትመለስ ቢጠይቋምትም ፈቃደኝነቷን አላሳየችም። ለማንኛውም በሊባኖስ የሚገኙ ናይጄሪያውያን እንደ ባርያ ሳይሆን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያዙ ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

ክስተቱንም ተከትሎ በሊባኖስ የቤት ስራ ለመስራት ለሚፈልጉ ናይጄሪያውያን የሊባኖስ ኤምባሲ ቪዛ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው ከናይጄሪያ እንዲሁም ከሌሎች አፍሪካ አገራት ታዳጊ በተለያየ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች በአዘዋዋሪዎች እንደሚሸጡ ነው።

ብዙዎችም በአውሮፓና በእስያ የተሻለ ስራ ታገኛላችሁ በሚል ከቤታቸው ተታለው ወጥተው በቤት ሰራተኝነት እንዲሁም በወሲብ ንግድ እንደሚሰማሩና ብዙዎችም ለብዝበዛ እንደሚዳረጉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

Comments