በአዲስ አበባ የኤልክትሪክ አውቶቡስን ስራ ላይ ለማዋል ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ አሳውቋል።
ቢሮው በውጭና ሀገር ውስጥ ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ለአውቶቡስ ግዥ የሚውል ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የኤልክትሪክ አውቶቡሶች ሌሊት ቻርጅ አድርገው ቀኑን በሙሉ ያለምንም የጊዜ ብክነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉ ያለው ቢሮው።
አውቶቡሶቹ የሙከራ ትግበራ የሚደረግባቸው በሸገር እና አንበሳ አውቶቡሶች ሲሆን ፥ ከሸጎሌ ዴፖ ቅርበት ያላቸው አራት ኮሪደሮች ልየታ መከናወኑም ተገልጿል።
የመጀመሪያው ኮሪደር ከአዲሱ ገበያ - ቄራ ሲሆን፥ ሁለተኛው ኮሪደር መነሻውን ዊንጌት አድርጎ መዳረሻው አየር ጤና ይሆናል።
እንዲሁም ሶስተኛው ኮሪደር ከለገሃር ተነስቶ መዳረሻው ድል በር እንዲሁም አራተኛው ኮሪደር ከአውቶቡስ ተራ - አስኮ ይሆናል፡፡
ከዴፖው ያላቸው ርቀት፣ ከBRT ኮሪደሮች ጋር ያላቸው ትስስር እና ገበያ አካባቢዎች መሆናቸው ለኮሪደሮች የሙከራ ትግበራ መመረጥ እንደመስፈርት ተቀምጧል፡፡
በቀጣይ በከተማዋ ሌሎች ተጨማሪ ኮሪደሮችን በማጥናት የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል።
