"እውነተኛ ክርስቲያን አባቱ ክርስቶስን ይመስላል፡፡ ይሰደዳል እንጂ አያሳድድም፡፡ ይሰደባል እንጂ አይሳደብም፡፡ የጠፉትን ፍለጋ ይደክማል እንጂ ይባስ ብሎ አይገፈትርም፡፡ በወንድሙ ውድቀት ያለቅሳል እንጂ አይደሰትም፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን አባቱ ሌላ ነው፡፡

ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና በጊዜውም ያለ ጊዜውም ሊሆን ይገባል፡፡ ባገኘን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ባጣንም ጊዜ፤ ባለጤና በሆንን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በታመምንም ጊዜ፤ ሲሳካልን ብቻ ሳይሆን ባልተሳካልንም ጊዜ ማመስገን መለማመድ አለብን፡፡ የምስጋናችን ምንጭ የሁኔታዎች መለዋወጥ ሳይሆን ስለ አምላካችን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ ስንለማመድ በክብር ላይ ክብር ይጨመርልናል፤ እንደ አባታችን ኢዮብ የዲያብሎስን አፍ እንዘጋለን፡፡

ተአምራትን ማድረግ ትፈልጋላችሁን?” እንኪያስ "በዘፈን የደነቆረን ጀሮ መዝሙር እንዲሰማ አድርጉት፡፡ ሴትን በመመኘት የታወረው ዐይን ፈጣሪውን እንዲያይ አድርጉት፡፡ በስርቆት የሰለለ እጅ በምጽዋት እንዲዘረጋ አድርጉት፡፡ ወደ ኃጢአት ቤት በመሄድ ሽባ የሆነውን እግር ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲሮጥ አድርጉት፡፡ ሐሜትን በማውራት ዲዳ የሆነውን ከንፈር መልካም ንግግርን እንዲናገር አድርጉት፡፡ ከተአምራት ሁሉ የበለጠ ተአምር ይሄ ነው፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ